top of page

ደብዳቤ

  • Writer: nejatahmedjuhar
    nejatahmedjuhar
  • May 14, 2019
  • 2 min read

ይድረስ… ለስንት ወራት ደብዳቤ እጽፍልሃለሁ ብዬ ወረቀቴን ሳነሣ እስኪርቢቶዬ ሲጠፋ፤ እስኪቢርቶ አገኘሁ ስል ደግሞ ወረቀት ሳጣ… እንዲሁ አልሞላልሽ ብሎኝ ሳልጽፍልህ ለቀረሁት ለሦሪያው ወንድሜ!

ለመሆኑ ግን እንዴት ነህ? አልፎ አልፎ እኮ ጎደኞችህን አገኛቸዋለሁ። ታዲያ ስለደህንነትህ ስጠይቃቸው እንዴት በሰቀቀን እንደሆነ ከላይኛው በቀር ማንም አያውቅም። ካሁን አሁን መርዶ ነገሩኝ አልነገሩኝ እያልኩ እሳቀቃለሁ። ግን አልሐምዱሊላህ እስካሁን ‹‹ሞተ›› ያለኝ የለም። ‹‹የት እንዳለ አናውቅም›› ነው የሚሉኝ። እኔም ትኖራለህ በሚል ተስፋ ይኸው እጽፋለሁ...!

‹‹እንዴት ነሽ? እንዴት ከረምሽ?›› ብለህ እንዳትጠይቀኝ…. ጊዜው እንዴት እንዳለፈ ሳስታውሰው እንዴት ይዘገንነኛል መሰለህ! በነገራችን ላይ… ያን ጊዜ ለዚያራ መጥተህ እኛ ሰፈር ያየኸው ድንኳን እኮ እስካሁን አልተነሣም! ‹‹በአገረ ሊቢያ ወንድሞቻችን ተገደሉ›› ብዬህ መጥተህ ለቅሶ ደርሰኸኝም አልነበር?! ከዚያ ጊዜ ጀምሮኮ ድንኳኑ አሁንም አለ። የሟች ቁጥር ይለያያል እንጂ ድንኳኑ ሁሌም ሙሉ ነው። የዓረብ አገር እኅቶቻችን መርዶ ቀጠለ .... ‹‹ከዚያስ›› አትልም? … ከዚያማ በኢሬቻ በዓል ላይም የሟች ቁጥር ቀጠለ …. አሁን ደግሞ በቅርቡ የቆሼ ሰፈር ቆሻሻ ተደርምሶ ሕፃን አልቀረ አዋቂ ፀጥ! ‹‹ምን? ቆሻሻ ሰው ገደለ?!!!›› ብለህ እንዳትገረም…. ‹‹እንኳን ሰው ቆሻሻ ጨክኖብናል›› ስልህ!! ሆሆሆ…

እናልህ ብሄራዊ የሐዘን ቀን ከሚሌኒየም ግባችን አንዱ መስሎ ቁጭ ብሏል፡፡ ‹‹ብሄራዊ የሐዘን ቀን ሳይሆን ብሄራዊ የጸሎት ቀን ነው የሚያስፈልገው!›› ብል እኔንማ ማን ይስማኝ ወንድምዬ!

ይህን ሁሉ የምዘከዝክልህ ‹‹ለቅሶ ያልደረስኩህ ለዚህ ነው›› ብዬ ለማሳበብ አይደለም፡፡ በጭራሽ!! ግን በቃ እወቀው ብዬ ነው። እንደእኔ እንደእኔማ ሐሳብ የሰፈራችን ድንኳን ሲነሣ ከጎረቤት ሱዳን ጀምሬ፣ በየመን እና በርማ አልፌ አሌፖ (ሦሪያ) ለመምጣት እና ለማጽናናት ነበር ... ምን ዋጋ አለው… ነበር ሆኖ ቀረ እንጂ!

እንግዲህ ከፈለግክ ጨካኝ በለኝ…፤ ከፈለግክ ‹‹ራስ ወዳድ›› በለኝ…፤ ‹‹እንዴት እስካሁን ሳትጠይቂኝ›› ብለህ ተቆጣ…፤ ልክ ነህ! አንዴ በቲውተር አንዴ በፌስቡክ ምን ያህል ስቃይ ላይ እንደሆናችሁ ለዓለም ሕዝብ ስታሳይ እኔም አይቶ ካላዩት በመሆኔ እንዴት እንደማፍር ኣትጠይቀኝ። ይህን ሁሉ በደል በቻልክ አሁን ደግሞ የኬሚካሉን ጨመሩብህ! ከወደ አሜሪካ ሚሳኤሎችን የዓመት በዓል ስጦታ ይመስል በላይ በላይ አወረዱብህ! ለካስ የ40 ቀን እድልን ለማማረር ራሱ የአርባ ቀን እድል ያስፈልግ ኖሯልና!

የሦሪያው ወንድሜ… አሁን እንኳዋ አገኝሃለሁ የሚል ተስፋዬም መንምኗል። ግን እንደው አፈር ስሆን ወንድም አለም አንዲት ነገር ልጠይቅህማ...... እንደው ድንገት ብንገናኛ..... ቢሆን በዱንያ ካልሆነ ደሞ ከዚያኛው አለም......... እና ያኔ.....ይህን ሁሉ ነገር አይቶ ባላየ አልፌ ለይቅርታ ብመጣ ይቅር ትለኝ ይሆን ይሆን?

Comentarios


© 2023 by Jessica Priston. Proudly created with Wix.com

bottom of page