top of page

የማሚዬ አብሽ ውስጤ ነው!!!

  • Writer: nejatahmedjuhar
    nejatahmedjuhar
  • May 15, 2019
  • 1 min read

የዘንድሮ ረመዳን እኮ ሳናስበው ሄደ፡፡ ሄደ ሳይሆን ሮጠ ብል ይቀላል ለነገሩ! ከረመዳን ቀጥሎ በሚመጣው ተወዳጁ የዒድ በዓል ዙሪያ እንድንጨዋወት አስቤ ነው እስኪርቢቶ ፈልጌ ያነሣሁት፡፡ (‹‹ፈልጌ ያነሣሁት›› ያልኩት በቤታችን ከሰኔ በኋላ እስኪርቢቶ ማግኘት የስኳር ድርጅታችን ያጠፋውን 70 ቢሊየን ብር የማግኘት ያክል ከባድ ስለሆነ ነው! lol)

በቤታችን ዒድን ዒድን ከሚያስመስሉት ነገሮች አንዱ አብሽ ነው። አዎ… ያውም የማሚዬ አብሽ! ‹‹አብሽ ምንድን ነዉ!!??›› ላላችሁ ‹‹ውሃ እና አብሽን በማደባለቅ የሚሠራ ቆንጆ መጠጥ ነው›› ብያለሁ፡፡ ውሃ በአብሽ ደብለቅ አድርጎ ሲባል ቀለል ይመስላችሁ ይሆናል። በጭራሽ ቀላል አይደለም። እንኳን ለለማጅና ልምድ ላላት እናቴ እንኳን ቀላል አይደለም። እንዴት ካላችሁኝ... እንዲህ እላችኋለሁ...

ከእለታት በአንዱ ዒድ በአብሽ ላይ ታሪካዊ ስህተት ተፈጸመ። ነገሩ እንዲህ ነው... ማሚ አብሹን በውሃ ስትዘፈዝፈው አብሹን በጣም አብዝታው ነበር ባጋጣሚ። እኛ ልጆቿ አብሹን እንዳበዛች ስንነግራት ‹‹...ዝም በሉ እኔ ነኝ የማውቀው! የሃያ ዓመት ልምድ እኮ ነው ያለኝ እናንተ!!!›› ብላ ምክራችንን ከቁብ ሳትቆጥር አብሹን ክምር ክምርምር አደረገችዋ! በኋላ ላይ አብሹ ሲመታ (አብሽ ከተዘፈዘፈ በኋላ በእጅ ወይ በማሽን ይመታል) ለአንድ ባልዲ ነይታ የሠራችው አብሽ ሦስት ባልዲ ሆኖ ቁጭ አለ! ከዒድ በኋላ ቤት እንድንቀመጥ ማን ይፍቀድልን! ከልክ በላይ የበዛውን አብሽ አንዴ ፋጡማጋ…. አንዴ ትእግስትጋ.... እየተላክን ማዞር ሥራችን ሆነ!

ዒድ ሲመጣ በጉጉት የምጠብቀውን አብሽ ከዚያች ቀን በኋላ በጉጉት ብቻ ሳይሆን በፍርሃትም ጭምር ነው የምጠብቀው። ‹‹ደሞ ድንገት በዝቶ ይዛችሁ ዙሩ እንባል ይሆን?›› እልኩ እሳቀቃለሁ። እናላችሁ ዘፈን ያልተዘፈነለት፣ ግጥም ያልተገጠመለት ብቸኛ መጠጥ አብሽ ይመስለኛል። አብሽ ውስጤ ነው! በተለይ የማሚዬ ውስጤ ነው!!!!!

Comments


© 2023 by Jessica Priston. Proudly created with Wix.com

bottom of page